03/11/2017
Pleas read this heart breaking poem to our lady st virgn mery
አዶናይ ቅርብሽ ነው
♥♥♥♥♥
በሊቃናቱ አፍ__ የምትወደሽ
በቅዱሳኑ ዘንድ__ ከፍ ያለው ክብርሽ
የመላእክት እህት__እያልን የምንጠራሽ
የንፀኋን አክሊል__ሶልያና አንቺ ነሽ።
የቃለ እግዚአብሔር __ ማደሪያ አትሮንሱ
ከፍጥረት ለይቶ__ መረጠሽ ንጉሡ
ድንግልም እናትም __ሆነሻል ማርያም
አክብሮሻል አምላክ__ እስከ ዘለአለም።
ነቀፋ የራቀሽ__ የሌለብሽ ነውር
የመቅደሱ እንግዳ__የሕግ ደቀ መዝሙር
የመለኮትን ጸጋ__የለበስሽ በፍቅር
የነቢያት ዜና__የእውነት መነጽር።
ጌታ ካንቺ ጋር ነው__ ይድረስሽ ውዳሴ
ፀጋን የተሞላሽ__ ታመስግንሽ ነፍሴ
ጽኑ ቃል ኪዳንሽ__የነጻነት ልብሴ
አማላጅነትሽን__ ያውጃል ምላሴ።
ሰውነትሽ ንጹሕ__የምድር መቅደስ ነው
ዘር ያልተዘራበት __እርግማን የራቀው
በኃጢአት ምክንያት __ ሞት ቢሰለጥንብን
እንዳንጠፋ ፈቅዶ__ አንቺን አስቀረልን
ኢሳይያስ እንዳለው__ ከገሞራው ዳንን።
ፍጹም ንጽሕናን__ከላይ የተጎናጸፍሽ
እውነተኛው መና__ ሲሳይን የታቀፍሽ
አንቺን ከማን ጋራ__ ከቶ ላነጻጽርሽ?
በቃል ኪዳን ከሁሉ በላይ ነሽ።
የእግዚአብሔር መልእክተኛ__ አብሳሪው ገብርኤል
ሠላምታን ሲዘራ__ተልኮ ከልዑል
ባንቺ ያድራልና__ ቅዱስ አማኑኤል
በሎ ጀመረልሽ __ ተፈስሒ ድንግል።
በምድርም ተሰማ __ ሰማያዊው ደስታ
ቅድስት ኤልሳቤጥም __ ጮኽች አሰምታ
የጌታዬ እናት__ ወደ እኔ እንዴት መጣሽ?
ደንግል እናቴ ሆይ__ ከሴቶች ልዩ ነሽ።
ነውሬ ተወግዶ__ ጌታዬ ጎብኝቶኝ
ስላደረገልኝ __ለምስጋና ቆምኩኝ
የሰላምታ ድምጽሽን __ አንደሰማሁኝ
በመንፈስ ቅዱስ ኃይል__ሐሴት ለበስኩኝ።
በሆዴ ውስጥ ያለው__ የስድስት ወሩ ጽንስ
ሠገደ ለአምላኩ__ወልደ ዘካርያስ
ክብርና ምስጋና__ ለሥላሴ ይድረስ።
ሠማይና ምድር__ የማይሸከሙት
የዓለም ፈጣሪ__አምላከ አማልእክት
በዚች ብላቴና__ተወስኖ ስናይ
እጅግ ያስደንቃል__ጥበቡ የአዶናይ።
እንመሰክራለን__ አውጀን እውነት
እንናገራለን__ በምንሔድበት
የጌታን ማደሪያ__ ክብር እንዳላት
ልክ እንደ ትላንቱ __እንደተመረጡት።
ጥንት የነበረው__መድኃኒዓለም
ዘመን ሳይቆጠር__አለ በማርያም
ከፍጥረታት በፊት__በእግዚአብሔር ሕሊና
ወለተ ኢያቄም__ ታስባለችና።
በተወዳጅ ክንዷ__ ሕፃኑን ታቅፋ
በክብር ላይ ክብርን__ ማርያም ተጎናጽፋ
ትውልድን ስታስምር__በሞት እንዳይጠፋ
ኪዳነምሕረት__የአዳም ልጆች ተስፋ
አለች በሠማያት__ በወርቅ ተጽፋ።
ከዘመነ አዳም__ እስከ ምጽአት
በብሩካን ጻድቃን__በአበው አንደበት
የነቢያት ዜና__ የሐዋርያት ደስታ
ሰምሽ የሚጠራ__በቅዱሱ ቦታ
ሐረገ ወይን ድንግል__ የሰላም አንድምታ።
ቀድሞ የተጠሩት__በወንጌል ያመኑ
የተመረጡትም __ ከቅስፈት የዳኑ
ከብረው የጸደቁት__ በቃል የመነኑ
አንቺን ለማወደስ__ በቅኔ ተካኑ
የመስቀሉን ፍቅር__ እያመሰገኑ።
በደጀ ሰላምሽ__ በዝክርሽም ስፍራ
በዕንባ በጸሎት __ ስምሽን ስንጠራ
ፈጥነሽ ድረሽልን__ ከቦናል መከራ
ብልጣሶር ታብይዋል__ ልቦናችን ፈራ።
በከብቶቹ ግርግም__ በዚያ የታቀፍሽው
በግብጽ በረሃ__ በጀርባሽ ያዘልሽው
የምሕረት ባለቤት__እኛ የምናመልከው
ይማረን አሳስቢ__ ፊቱን ይመልሰው
ድንግል ማርያም ሆይ__አዶናይ ቅርብሽ ነው።