07/12/2021
የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላ
| ዛሬና ትናንት የብዙ ሰዎችና የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት የሳበ ጉዳይ በመሆኑ የግል ምልከታዩ እነሆ:-
ዜጎች ሰርቶ የመብላት መብታቸውና ሕልውናቸውን የማስቀጠል መብታቸው በመመርያ የማይጣስና የማይገሰስ ነው።
የመንግስት አንዱና ዋነኛው ተግባር ዜጎች ሰርተው የሚኖሩበት ሁኔታዎች ማመቻቸትና እድል መፍጠር ነው፡፡ መንግስት 'ራሱ የስራ እድል መፍጠርም ሆነ በግል ዘርፉ አማካኝነት ስራን ማመቻቸት ካልቻለ፣ ዜጎች ለእርዳታ ተቀባይነትና ለማህበራዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ ሲባል ኢ- መደበኛ ስራዎችን ቢቻል ከታክስ ነጻ በማድረግ ወይም በጣም በዝቅተኛ ታክስ ሰርተው የመኖር "እድል" ሊነፍጋቸው አይገባም፡፡
ይህ ደግሞ ከጎረቤቶቻችን ጀምሮ በብዙ ሀገሮች የተለመደ ነው።
Reserve Army of labour ከሚባለው ሁልቆ መሳፍርት የሌለው ስራ አጥ በተጨማሪ፣ ኢትዮጵያ በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን በላይ ለሆኑ ዜጎቿ የስራ እድል መፍጠር ይጠበቅባታል፡፡
እንደሚታወቀው ግን ሀገራችን እንኳን አዲስ የስራ ፈላጊውን ይቅርና ለነባሩ ስር አጥም በቂ የስራ እድል ማፍጠር የቻለች ሀገር አይደለችም፡፡
ይህ ነባራዊ ሀቅ ባፈጠጠባትና ባገጠጠበት ሀገር ተቆጥረው በገደብ እንዲገቡ በሕግ የተፈቀዱ አልባሳትና ቁሳቁሶችን እጅግ ፈታኝ በሆነ መንገድ ጥሪት አብቃቅተው ትንሽ ትርፍ ለማግኘት ከሚበላ፣ ከሚጠጣና ከትራንስፖርት ቆጥበውና ተዳብለው እያደሩ ቤተሰቦቻቸውን ዳቦ ለማብላት የሚታገሉ በተለምዶ የሻንጣ ሰራተኛ የሚባሉ ኢ-መደበኛ ለፍቶ አዳሪዎችን፣ በዚህ ፈታኝ ጊዜ ስራቸውን ማገድ ስራ አጥነትን በማባባስ ማህበራዊ ቀውስንና ሁከት ከመቀስቀስ ውጭ ምን ትርፍ እንዳለው ለመገመት አዳጋች ነው፡፡ ዜጎች እኩል ናቸው በሚባልበት ሀገር ስሞታቸው በልዮነት የተሰማላቸው አስመጭዎችስ በተለይ የውጭ ምንዛሪ የማግኘት፣ የማስመጣትና ዝቅተኛ ታክስ የመቀረጥ ሞኖፖሊ እንዴት ሊኖራቸው ቻለ?
መንግስት እነዚህን አነስተኛና ጥቃቅን እቃዎችን በመቅረጥ ከሚያገኘው ገቢ ይልቅ ኢ- መደበኛው ስራ ከሚፈጥረው የስራ እድል፣ ከስራ እድሉ ከሚገኘው ግብርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከሚሰበስበው ገንዘብ ወዘተ ጋር ሲነጻጸር የተሻለ መሆኑ በየትኛው ጥናት ተፈትሾና ሚዛን ደፍቶ መንግስትን ጎድቷል፣ በዝብዟል እንዳስባለ ግራ የሚያጋባ ነው ? መንግስት ማለት ሕዝብ መሆኑንስ እንዴት ተረሳ? የተራበ፣ በማህበራዊ ቀውስ የተመታ፣ በድህነት ክብሩን ያጣ ተመጽዋች ዜጋ የሞላበት ሀገርና መንግስት ላይ የሚካሄደው ዓይን ያወጣ ተጽእኖ ምን እንደሆነ በግልጽ እየታየ እንደዚህ ዓይነት አካሄድ መከተል ለምን ተመረጠ? እድሜው ለስራ ከደረሰው ከከተማ ነዋሪ ውስጥ 50 % ስራ አጥ ሆኖ እያለ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገድ ስራ የፈጠረ ዘርፍን ማሻሻልና ማጎልበት እየተቻለ ያለ ቅድመ ሁኔታና ዝግጅት በማገድ ተጨማሪ ዜጎችን ስራ አጥና ምጽዋተኛ በማድረግ ወዴት ለመድረስ ይታሰባል ? አፋጣኝ መልስ የሚሻ ጉዳይ ነው?!
በዚህ ፈታኝ በሆነና ስራ በተዳከመበት፣ ኢኮኖሚው በተናጋበት፣ ኑሮ በተወደደበት፣ እቃ በጠፋበት፣ የአጉዋ ተጠቃሚና ሌሎች ሰራተኞችን ከስራ በማፈናቀል ሁለንተናዊ ቀውስ ለመፍጠር ሴራ በሚሸረብበትና መንግስት የሕዝብን ድጋፍ በከፍተኛ ደረጃ በሚሻበት ወቅት በድንገት ይህንን ዓይነት ውሳኔ መወሰን ሕዝባዊነቱና ለመንግስት ተቆርቋሪነቱስ ምኑ ላይ ይሆን ?
እስኪ መለስ ብለን ደግሞ ገቢዎች በዚህ ደረጃ የተማረረበትና ዜጎችን አምርሮ የተቆጣበት የሻንጣ ስራ ተጠቃሚዎች እነማን እንደሆኑ እንፈትሽ ?
-ዋነኛው የአየር መንገድ ሲሆን አንዱና ከፍተኛ ገቢ በሻንጣ ስራ የተሰማሩ ዜጎችን ማመላለሱ ነው፡፡
-ቀጥሎ የትኬት ሽያጭ ቢሮዎች አሉ
-የሻንጣ ሸቀጥ አስመጭው ዜጋ (ተመላላሽ)
-ሸቀጡን የሚረከበው ሱቅና በሱቁ ውስጥ የተቀጠረው፣ ሱቅ በደረቴውና የመንገድ ዳር ነጋዴ ...
-የሻንጣ ስራውን ለመከወን በስደት የሚገኙ ዜጎች
-የሻንጣ ነጋዴዎችን የሚያመላልሱ ታክሲዎች
-ሱቅ አከራዮች
-የጉምሩክ ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸው ወዘተ ናቸው፡፡
እንግዲህ ከአየር መንገድ ውጭ እነዚህ ሁሉ ዜጎች የመንግስትን እጅ ሳይጠብቁ ከእጅ ወደ አፍ ቢሆንም ሆዳቸውን ለማሸነፍ የሚታትሩ ዜጎች ናቸው። ክልከላው አስፈላጊ ከሆነ እነዚህ ዜጎች ሕልውናቸውን ለማስቀጠል አማራጩ ምንድን ነው?!
የሻንጣ ስራ ለምን የስራ እድል ሊሆን ቻለ? የሻንጣ ኢ-መደበኛ ስራ የግድ የስራ እድል የሆነበት ምክንያት ጉምሩክ የገቢ ቀረጥን በመሰብሰብ ዙርያ ከሚታማበት ሙስና ይጀምራል። ቀጥሎ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጦት፣ የቫት ደረሰኝ የማይቆርጡ ነጋዴዎች ተጽእኖ፣ ነጋ ጠባ ብለው ዋጋ የሚቆልሉና እየተመሳጠሩ የገቢም ሆነ የትርፍ ግብር የማይከፍሉ አስመጭዎች ውድድሩን ከንቱ ማድረጋቸውና ውዳቂና ርካሽ ሸቀጥ ያለ አማራጭ በገፍ የሚግበሰብሱና የግብይት ስርዓቱን በሞኖፖሊ የተቆጣጠሩ አስመጭዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ምሳሌያዊ ንጽጽር። ዛሬ ፋና ላይ እንደሰማሁት ከሆነ በጣት የሚቆጠሩ አስመጭና አከፋፋይ ነጋዴዎች ከ32 ነጥብ 5 ቢሊየን (የተደረሰበት ነው እንግዲህ) ብር በላይ በሕገ ወጥ መንገድ ደረሰኝ ባለመቁረጥና ሀሰተኛ ደረሰኝ በመስጠት ግብይት በመፈጸማቸው ተከሰው 8 ሚሊየን ብር ብቻ አስተዳደራዊ ቅጣት ተቀጥዋል፡፡ ይህ ገንዘብ የሀገሪቱ በጀት 6 በመቶ ሲሆን የሕዳሴን ግድብን 1/3 ገደማ ይሸፍናል።
ንጽጽሩን እንቀጥል። ሀገሪቱ ውስጥ የሚመላለሱ የኢ-መደበኛ የሻንጣ ነጋዴዎች እንዲያስገቡ በቁጥር የሚፈቀድላቸው 29 አነስተኛና ጥቃቅን ሸቀጥና አልባሳት አይደለም፤ በዚህ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ሃይሎች የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሚያስገቡት ገቢ ቢደመር መንግስት በሕገ ወጥ ነጋዴዎች ያጣውን 32 ነጥብ 5 ቢሊየን 10 በመቶ አያክልም፡፡ ጥቂቶች 325 ቢሊየን ብር በሕገ ወጥ መንገድ ግብይት ፈጽመው 8 ሚሊየን ብር ይቀጣሉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቀጠሩ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ኢ- መደበኛ ስራ ሰርተዋል በሚል ያውም ሕገ ወጥ ሳይሆኑ በአንድ መስርያ ቤት መመሪያ በሕገ ወጥነት ይፈረጃሉ፣ ተግባራችሁ በሕግ ያስጠይቃል ይባላሉ።
በዜጎች መካከል እንደዚህ ዓይነት ልዩነት እየፈጠሩ በፍርደ ገምድልነት ማህበራዊ ቀውስ ማስፋፋትና ቤተሰብ መበተን? በየትኛው የሕገ መንግስቱና ሕግጋቶቹ ላይ ለየትኛው ባለስልጣንና ሹመኛ የተሰጠ ስልጣን ይሆን?! ስራ ለመፍጠር አቅምና ብቃት የሌለው ሀይል የብዙዎች እንጀራ የሆነውን ኢ- መደበኛ ስራን ለማፍረስና ያለ ቅድመ ዝግጅትና አማራጭ ቤተሰብ ለመበተን የሞራል ልዕልናውንስ ከየት አገኘው?!
***
የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ የገቢ ዕቃዎች ክልከላና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ለኢትዮጵያ ቼክ የሰጠው ማብራሪያ!
ባለፉት ሁለት ቀናት የግል መገልገያ እቃዎች መመሪያ ቁጥር 51/2010 አፈጻጸም መታገድን የሚያትት ደብዳቤና ለተመላላሽ ነጋዴዎች ደግሞ ምንም አይነት እቃ (አልባሳትና ጫማን ጨምሮ) ወደ ሀገር ይዞ መምጣት መከልከሉን የሚያሳስብ ማስታወቂያ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሲዘዋወሩ ተመልክተናል።
በርካታ ተከታዮቻችንም የመረጃዎቹን ትክክለኛነት እንድናጣራ ጠይቃችሁናል።
ኢትዮጵያ ቼክ ጉዳዩን በተመለከተ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ድንበኞች ትምህርት ቡድን አባል የሆኑትን አቶ ምትኩ አበባዉ ያናገረ ሲሆን እርሳቸዉም “ደብዳቤዎቹ ከኛ ነዉ የወጡት፤ ትክክለኛ ናቸዉ” ብለዉናል።
የዚህ ክልከላ ምክንያትም ለንግድ የማይዉሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ዝርዝር ለመወሰን የወጣዉን መመሪያ 51/2010ን በመጠቀም በተመላላሽ መንገደኞች ከቀረጥ ነጻ የሚገቡ ነገር ግን ለንግድ አላማ እየዋሉ የሚገኙ ዕቃዎች በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ ጫና በመፍጠራቸዉ መሆኑን ነግረዉናል።
“አንድ መንገደኛ ሁሌ የሚመላለስ ከሆነ ያለቀረጥ ሁሌም እየተመላለሰ የሚያመጣ ከሆነ በህጋዊ መልኩ በኮንቴነር የሚያስጭኑና ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎችን ኪሳራ ዉስጥ የሚያስገባና ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑ ይህ ደብዳቤ ወጥቷል” ብለዋል።
የግል መገልገያ ዕቃዎች መመሪያ ቁጥር 51/2010 ስራ ላይ መዋሉን ተከትሎ በተለይም አልባሳትና ጫማዎች በብዛት ወደ ሀገር ዉስጥ መግባት መጀመራቸዉና ከህጋዊ ነጋዴዎችም አቤቱታና ተቃዉሞ ሲቀርብ መቆየቱን አቶ ምትኩ አበባዉ ይናገራሉ።
“ንግድ ፍቃድ ያለዉ ሁሉ እየዘጋ በዛ እስከማምጣት ድርሷል። ምክንያቱም ቤት ተከራይቶ፤ ቀረጥ ከፍሎ፤ ግብር ከፍሎ አላዋጣዉም። ስለዚህ በመንገደኛ ያለቀረጥ እያስገባ ንግድ ፍቃዱን እያዘጋ በዛ እስከማምጣት የደረሰበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ” ብለዋል።
ስለዚህም በአዲሱ ዉሳኔ መሰረት “ማንኛዉም መንገደኛ ማንኛዉንም አልባሳትም ሆነ የንግድ ባህሪ ያለዉ ዕቃ ይዞ ከመጣ ቀረጥና ታክስ መክፈሉ እንደተጠበቀ ሆኖ በወንጀል ምርመራ ህግም እስከ ማስጠየቅ ድረስ የሚደርስ ነዉ” ብለዋል።
ነገር ግን ከሀገር ዉጪ ከአንድ ወር በላይ የቆዩና ተመላላሽ ያልሆኑ የመጀመሪያ መንገደኞች፤ ቱሪስቶች እና ዲፕሎማቶች ፓስፖርታቸዉና ማህደራቸዉ ታይቶ የንግድ ባህሪ የሌለዉ ዕቃ የያዙ ከሆነ ለጊዜዉ በመመሪያ 51/2010 መሰረት የሚስተናገዱ መሆኑን አቶ ምትኩ አበባዉ ነግረዉናል።
“ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ማንኛዉም መንገደኛ ከቀረጥ ነጻ ይዞ እንዲገባ የተፈቀዱ ዕቃዎችን (የተዘጋጁ አልባሳትና ጫማዎችን ጨምሮ) ተገቢዉን ቀረጥና ታክስ መክፈል እንደተጠበቀ ሆኖ ለንግድ እላማ የሚዉል ነዉ ተብሎ ከታመነ ለመጀመሪያ ጊዜ በቅጣት (እጥፍ ቀረጥና ታክስ) ይስተናገዳል። ለሁለተኛ ጊዜ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ግን በወንጀል መጠየቅ ድረስ የሚያስደርስ ነዉ” ብለዋል።
ጠቅልለዉ ወደ ሀገር ቤት የሚመለሱ መንገደኞች ደግሞ ጓዞቻቸዉን ይዘዉ ቢመጡም ሆነ በካርጎ ቢልኩ በመመሪያ 51/2010 የተፈቀደና ሲገለገሉበት የቆየ ዕቃ ከሆነ ከቀረጥ ነጻ ማስገባት ይችላሉ። ይሁን እንጂ በመመሪያዉ ከቀረጥ ነጻ እንዲገቡ የተፈቀዱ ቢሆኑም ዕቃዎቹ አዳዲስ እስከሆኑ ድረስ ቀረጥና ታክስ እንደሚከፈልባቸዉ ተነግሯል።